Revelation of John 2

በኤፌሶን ላለው ቤተ ክርስቲያን

1 “በኤፌሶን ላለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ
ወይም መልእክተኛ ፤ እንዲሁም 8፣ 12 እና 18
እንዲህ ብለህ ጻፍ፤

ሰባቱን ከዋክብት በቀኝ እጁ የያዘው፣ በሰባቱም የወርቅ መቅረዞች መካከል የሚመላለሰው እንዲህ ይላል፤

2 ሥራህን፣ ጥረትህንና ትዕግሥትህን ዐውቃለሁ። ክፉዎችንም ችላ ብለህ እንዳላለፍሃቸው፣ ሐዋርያት ሳይሆኑ ሐዋርያት ነን የሚሉትንም መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው ዐውቃለሁ። 3ደግሞም በትዕግሥት መጽናትህንና ስለ ስሜም መከራ መቀበልህን ዐውቃለሁ፤ በዚህ ሁሉ አልታከትህም።
4 ይሁን እንጂ የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ ይኸውም የቀድሞውን ፍቅርህን ትተሃል። 5እንግዲህ ከየት እንደ ወደቅህ ዐስብ፤ ንስሓ ገብተህ ቀድሞ ታደርገው የነበረውን ነገር አድርግ፤ ንስሓ ካልገባህ፣ መጥቼ መቅረዝህን ከቦታው እወስድብሃለሁ። 6ነገር ግን ይህ በጎ ነገር አለህ፤ እኔ የምጠላውን የኒቆላውያንን ሥራ አንተም ጠልተሃል።
7 መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን፣ ጆሮ ያለው ይስማ፤ ድል ለሚነሣ በእግዚአብሔር ገነት ካለው ከሕይወት ዛፍ እንዲበላ አደርገዋለሁ።

በሰምርኔስ ላለው ቤተ ክርስቲያን

8 “በሰምርኔስ ላለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤

የመጀመሪያውና የመጨረሻው፣ ሞቶም የነበረውና ሕያው የሆነው እንዲህ ይላል፤

9 መከራህንና ድኽነትህን ዐውቃለሁ፤ ይሁን እንጂ ሀብታም ነህ፤ አይሁድ ሳይሆኑ አይሁድ ነን እያሉ ስምህን የሚያጠፉትን ዐውቃለሁ፤ እነርሱ ግን የሰይጣን ማኅበር ናቸው። 10ሊደርስብህ ያለውን መከራ አትፍራ። እነሆ፤ ዲያብሎስ ሊፈትናችሁ አንዳንዶቻችሁን ወደ እስር ቤት ይጥላል፤ ዐሥር ቀንም መከራ ትቀበላላችሁ። እስከ ሞት ድረስ ታማኝ ሁን፤ እኔም የሕይወትን አክሊል እሰጥሃለሁ።
11 መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ፤ ድል የሚነሣም በሁለተኛው ሞት ከቶ አይጐዳም።

በጴርጋሞን ላለው ቤተ ክርስቲያን

12 “በጴርጋሞን ላለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤

በሁለት በኩል የተሳለ ስለታም ሰይፍ ያለው እንዲህ ይላል፤

13 የሰይጣን ዙፋን ባለበት እንደምትኖር ዐውቃለሁ፤ ሆኖም ስሜን አጥብቀህ ይዘሃል። ሰይጣን በሚኖርበት በእናንተ ከተማ የተገደለው ታማኙ ምስክሬ አንቲጳስ በነበረበት ዘመን እንኳ በእኔ ያለህን እምነት አልካድህም።
14 ይሁን እንጂ የምነቅፍብህ ጥቂት ነገር አለኝ፤ የእስራኤል ልጆች ለጣዖት የተሠዋ ምግብ እንዲበሉና እንዲሴስኑ በፊታቸው መሰናከያ ያስቀምጥ ዘንድ ባላቅን ያስተማረውን የበለዓምን ትምህርት የሚከተሉ አንዳንድ ሰዎች በመካከልህ አሉ፤ 15የኒቆላውያንን ትምህርት የሚከተሉ ሰዎችም በአንተ ዘንድ አሉ። 16ስለዚህ ንስሓ ግባ፤ አለዚያ ቶሎ እመጣብሃለሁ፤ በአፌም ሰይፍ እዋጋቸዋለሁ።
17 መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል ለሚነሣ ከተሰወረው መና እሰጠዋለሁ፤ ደግሞም ከሚቀበለው ሰው በስተቀር ማንም የማያውቀው አዲስ ስም የተጻፈበትን ነጭ ድንጋይ እሰጠዋለሁ።

በትያጥሮን ላለው ቤተ ክርስቲያን

18 “በትያጥሮን ላለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤

እንደ እሳት ነበልባል የሆኑ ዐይኖችና በእሳት ቀልጦ የነጠረ ናስ የሚመስሉ እግሮች ያሉት የእግዚአብሔር ልጅ እንዲህ ይላል፤

19 ሥራህን፣ ፍቅርህን፣ እምነትህን፣ አገልግሎትህንና ትዕግሥትህን ዐውቃለሁ፤ ደግሞም ከመጀመሪያው ሥራህ ይልቅ የአሁኑ እንደሚበልጥ ዐውቃለሁ።
20 ይሁን እንጂ የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ ነቢይ ነኝ የምትለዋን ሴት ኤልዛቤልን ችላ ብለሃታል፤ እርሷ አገልጋዮቼ እንዲሴስኑና ለጣዖት የተሠዋ ምግብ እንዲበሉ በትምህርቷ ታስታቸዋለች። 21ከዝሙቷ ንስሓ እንድትገባ ጊዜ ሰጥቻት ነበር፤ እርሷ ግን ፈቃደኛ አልሆነችም። 22ስለዚህ በመከራ ዐልጋ ላይ እጥላታለሁ፤ ከእርሷም ጋር የሚያመነዝሩትን፣ ከመንገዷ ንስሓ ካልገቡ፣ ብርቱ ሥቃይ አመጣባቸዋለሁ፤ 23ልጆቿንም በሞት እቀጣቸዋለሁ። ከዚያም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እኔ ልብንና ሐሳብን የምመረምር መሆኔን ይረዳሉ፤ ለእያንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እከፍላችኋለሁ።
24 ትምህርቷን ላልተከተላችሁና የሰይጣንም ጥልቅ ምስጢር ነው የሚባለውን ላልተቀበላችሁ፣ በትያጥሮን ለቀራችሁት ለእናንተ ግን ይህን እላለሁ፤ በእናንተ ላይ ተጨማሪ ሸክም አልጭንባችሁም፤ 25ብቻ እኔ እስክመጣ ድረስ ያላችሁን አጥብቃችሁ ያዙ።
26 ድል ለሚነሣና ሥራዬንም እስከ መጨረሻው ለሚፈጽም በአሕዛብ ላይ ሥልጣን እሰጠዋለሁ፤ እርሱም፦ 27‘በብረት በትር ይገዛቸዋል፤ እንደ ሸክላ ዕቃም ይፈጫቸዋል፤’ ይህም ልክ እኔ ከአባቴ ዘንድ ሥልጣንን እንደ ተቀበልሁ ነው፤ 28እኔም የንጋትን ኮከብ እሰጠዋለሁ። 29መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።
Copyright information for AmhNASV